በዚህ ክፍል የመላእክትን አማላጅነት የምንማርበት መንገድ ንጽጽር ነው፡፡ ማንም ክርስቲያን ከመጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳ የሚችለው ነገር ሰይጣን በተፈጥሮው መልአክ መሆኑን ነው፡፡
‹‹የራሳቸውን አለቅነት ያልጠበቁትን መላእክት››፤ ‹‹ኃጢአትን ላደረጉ መላእክት››፣ ‹‹… የቀደመው እባብ ተጣለ:: ወደ ምድር ተጣለ :: መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ፡፡›› የሚሉት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዐረፍተ ነገሮች ምንም ግብራቸው ቢከፋ ሰይጣንና ሠራዊቱ ተፈጥሮአቸው መልአካዊ መሆኑን ያስረዱናል፡፡ (ይሁቁ.6፤ 2ጴጥ2.4፤ ራእ12.9)
ሰይጣን የሰው ልጆችን ይፈትናል፡፡ እንዲያውም ሰይጣን በቅዱስ ወንጌል
‹‹ፈታኝ›› ተብሏል፡፡ (ማቴ4.3) ይሁን እንጂ እንዳገኘው ደርሶ ሰዎችን የመፈተን መብት የለውም፡፡ ስለዚህ በሰዎች ላይ ላዘጋጀው ፈተና ፈቃድ ያገኝ ዘንድ ምን ጊዜም ፈጣሪን ይለምናል፡፡ ፈጣሪም ማንንም ሰው በዓቅሙ እንጂ ከዚያ በላይ እንዳይፈትን መመሪያ ሰጥቶ ይፈቅድለታል፡፡ ይህንንም ጉዳይ የሥራ ወይም የንግድ ፈቃድ አውጥቶ ለሥራ እንደ መሰማራት ልናየው እንችላለን፡፡