በዚህ ክፍል የመላእክትን አማላጅነት የምንማርበት መንገድ ንጽጽር ነው፡፡ ማንም ክርስቲያን ከመጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳ የሚችለው ነገር ሰይጣን በተፈጥሮው መልአክ መሆኑን ነው፡፡
‹‹የራሳቸውን አለቅነት ያልጠበቁትን መላእክት››፤ ‹‹ኃጢአትን ላደረጉ መላእክት››፣ ‹‹… የቀደመው እባብ ተጣለ:: ወደ ምድር ተጣለ :: መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ፡፡›› የሚሉት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዐረፍተ ነገሮች ምንም ግብራቸው ቢከፋ ሰይጣንና ሠራዊቱ ተፈጥሮአቸው መልአካዊ መሆኑን ያስረዱናል፡፡ (ይሁቁ.6፤ 2ጴጥ2.4፤ ራእ12.9)
ሰይጣን የሰው ልጆችን ይፈትናል፡፡ እንዲያውም ሰይጣን በቅዱስ ወንጌል
‹‹ፈታኝ›› ተብሏል፡፡ (ማቴ4.3) ይሁን እንጂ እንዳገኘው ደርሶ ሰዎችን የመፈተን መብት የለውም፡፡ ስለዚህ በሰዎች ላይ ላዘጋጀው ፈተና ፈቃድ ያገኝ ዘንድ ምን ጊዜም ፈጣሪን ይለምናል፡፡ ፈጣሪም ማንንም ሰው በዓቅሙ እንጂ ከዚያ በላይ እንዳይፈትን መመሪያ ሰጥቶ ይፈቅድለታል፡፡ ይህንንም ጉዳይ የሥራ ወይም የንግድ ፈቃድ አውጥቶ ለሥራ እንደ መሰማራት ልናየው እንችላለን፡፡
በዚህ መሠረት ሰይጣን ጻድቁ ኢዮብን ለመፈተን ሲያስብ ከመላእክት ጋር በእግዚአብሔር ፊት ተገኝቶ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ (ኢዮ1.6-22) ይህን ሐሳብ በተመለከተ ሌላም የማያሻማ ቃል በቅዱስ ወንጌል ተጽፏል፡፡ ‹‹ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥታችሁ ለመነ›› (ሉቃ22.31) አያችሁ! ይህ አሠራር አይለወጥም፡፡ ምእመናን! እኛ ባንረዳው ነው እንጂ ሰይጣን የሰው ልጆችን ሁሉ የሚፈትው ዘወትር በዚህ መንገድ እያለፈ ነው፡፡ አስቀድሞ ይለምናል ከዚያ በኋላ ባገኘው ፈቃድ መሠረት ይፈትነናል፡፡ ከምንችለው በላይ እንፈተን ዘንድ የማይፈቅድ ልዑለ ባሕርይ አምላካችን እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይድረሰው! አሜን!
ወደ ጥንተ ነገራችን እንመለስ፡፡ በዚህ ክፍል የጀመርነው ትምህርት የመላእክትን አማላጅነት ከሰይጣንና ከሠራዊቱ ተግባር ጋር እያነጻጸሩ ማየት ነው፡፡
ሰይጣን ክፉ መልአክ ሆኖ ሳለ እግዚአብሔርን እየለመነ እኛን ለመጉዳት የሚፈትነን ከሆነ ቅዱሳን መላእክት እኛን ከክፉ ነገር ሁሉ ለማዳን፣ ለመርዳትና ለመጥቀም ፈጣሪን አይለምኑትምን? ከለመኑትስ አማለዱ ማለት አይደለምን? እነርሱ ስለኛ ፈጣሪን የማይለምኑ ከሆነ የሰይጣንን ያህል ለተልኮአቸው አይተጉም ያሰኛል፡፡ ቅዱሳን መላእክት የእግዚአብሔር ልጆች ሆነው ሳለ እንደ ታናናሽ ወንድሞቻቸው የምንቆጠርና እንደ እነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች የሆንን እኛ ክርስቲያኖችን ለማዳን ፈጣሪን የማይለምኑት ከሆነ ከሚጎዳን ከሰይጣን በምን ይሻሉናል?
በዚህም ላይ ፈጣሪስ ቢሆን
እኛን ለመጉዳት እንዲለምነው ለሰይጣን ዕድል ሰጥቶት ቅዱሳን መላእክት ግን እንዳይለምኑት የሚቃወማቸው ይመስላችኋልን? ከክፉ ይልቅ በመልካም ነገር ደስ የሚሰኘው ልዑል አምላክ እንዲህ ሚዛኑን የሳተ ፈቃድ እንደሌለው እኛ ክርስቲያኖች ፈጽመን እናምናለን፡፡ ስለሆነም መላእክት በእውነት አማላጆቻችን ናቸው! እያልን ስንመሰክር እንኖራለን፡፡ አሜን!
ለማጠቃለል በቃል የሚጠና ሐሳብና ጥቅስ
ጽንሰ ሐሳብ፡- ሰይጣን መልአክ ነው፡፡ እርሱ ሰዎችን ለመፈተን ፈጣሪውን እንደሚለምን እስከታመነ ድረስ መላእክት የማያማልዱበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ሰይጣን ሰውን ለመጉዳት ቅዱሳን መላእክት ደግሞ ሰውን ለመጥቀም እግዚአብሔርን ይለምኑታል፡፡
1ኛ. ሰይጣን መልአክ ነው፡፡
(ይሁዳ ቁ6፤
2ጴጥ2.4፤ ራእ12.9)
2ኛ. ሰውን ለመፈተን ፈጣሪን ይለምናል፡፡
(ኢዮ1.6-22፤ ሉቃ22.31)
ይቆየን!
No comments:
Post a Comment