Monday, February 6, 2012

የቅዱሳን መላእክት አማላጅነት 5


በዚህ ክፍል የመላእክትን አማላጅነት የምንማርበት መንገድ ንጽጽር ነው፡፡ ማንም ክርስቲያን ከመጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳ የሚችለው ነገር ሰይጣን በተፈጥሮው መልአክ መሆኑን ነው፡፡ ‹‹የራሳቸውን አለቅነት ያልጠበቁትን መላእክት›› ‹‹ኃጢአትን ላደረጉ መላእክት›› ‹‹… የቀደመው እባብ ተጣለ:: ወደ ምድር ተጣለ :: መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ፡፡›› የሚሉት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዐረፍተ ነገሮች ምንም ግብራቸው ቢከፋ ሰይጣንና ሠራዊቱ ተፈጥሮአቸው መልአካዊ መሆኑን ያስረዱናል፡፡ (ይሁቁ.6 2ጴጥ2.4 ራእ12.9)
ሰይጣን የሰው ልጆችን ይፈትናል፡፡ እንዲያውም ሰይጣን በቅዱስ ወንጌል ‹‹ፈታኝ›› ተብሏል፡፡ (ማቴ4.3) ይሁን እንጂ እንዳገኘው ደርሶ ሰዎችን የመፈተን መብት የለውም፡፡ ስለዚህ በሰዎች ላይ ላዘጋጀው ፈተና ፈቃድ ያገኝ ዘንድ ምን ጊዜም ፈጣሪን ይለምናል፡፡ ፈጣሪም ማንንም ሰው በዓቅሙ እንጂ ከዚያ በላይ እንዳይፈትን መመሪያ ሰጥቶ ይፈቅድለታል፡፡ ይህንንም ጉዳይ የሥራ ወይም የንግድ ፈቃድ አውጥቶ ለሥራ እንደ መሰማራት ልናየው እንችላለን፡፡

Saturday, February 4, 2012

የቅዱሳን መላእክት አማላጅነት4


እስከዚህ ድረስ በሦስት ተከታታይ ክፍሎች የመላእክትን አማላጅነት ከመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ እየወስድን ተምረናል፡፡ ምንም እንኳን ማስረጃዎቹን ከመጽሐፍ ቅዱስ የጠቀስናቸው ቢሆኑም በምሥጢርና በምሳሌያዊ መንገድ የተቀመጡ ስለነበር ማብራሪያ የተሰጠባቸው ናቸው፡፡
ከዚህ ቀጥሎ የምንጠቅሳቸው ደግሞ በአንጻሩ በግልጽ የተቀመጡ መጽሐፍ ቅዳሳዊ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ የትምህርቱ ፍሰት ከከባድ ወደ ቀላልና ግልጽ ማስረጃ መሆኑን እየጠቆምኩኝ ወደ ትምህርቱ እወስዳችኋለሁ!
. ማስታረቅ መንፈሳዊ አገልግሎት ነው፡፡ ይህን የሚክድ ካለም ‹‹የማስታረቅንም አገልግሎት ከሰጠን›› የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ጠቅሰን አፉን እናሲዘዋለን፡፡ (2ቆሮ5.18) መላእክት ደግሞ አገልጋዮች ናቸው፡፡ ይህን ሲያስረዳ መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ቦታ ‹‹መላእክቱን መንፈስ የሚያደርግ፤ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል›› እያለ ሲጠቅሳቸው በሌላ ስፍራ ደግሞ ‹‹ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?›› ይላቸዋል፡፡ (መዝ103.4፤ዕብ1.14) ስለዚህ ማገልገል ማስታረቅን የሚያካትት ከሆነ መላእክት ደግሞ አገልጋዮች ከሆኑ አስታራቂዎች /አማላጆች/ መሆናቸውን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ነገረን ማለት ነው፡፡

Friday, February 3, 2012

የቅዱሳን መላእክት አማላጅነት3


በክፍል አንድና በክፍል ሁለት ትምህርታችን የመላእክትን አማላጅነት በተለያየ መንገድ ተመልክተናል፡፡ እነዚያን ያላነበባችሁ በፌስቡክ ኖት ውስጥ ያኖርኩአቸው በመሆኑ ያንን በመክፈት ማንበብ እንደምትችሉ ለመጠቆም እወዳለሁ!

ሦስተኛውን ክፍል እነሆ፡-
‹‹አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ›› ያለው የትንቢት ቃል ይፈጸም ዘንድ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው በምሳሌ አስተምሯል፡፡ /መዝ77.2/ በምሳሌ ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከል አንዱ የመላእክትን አማላጅነት የሚያሳይ ነው፡፡ ሙሉ የወንጌሉ ቃል ከዚህ ቀጥሎ የምናነበው ሲሆን ነጥቦቹን አንድ በአንድ እንመለከታለን፡፡

Thursday, February 2, 2012

የቅዱሳን መላእክት አማላጅነት 2


በክፍል አንድ ትምህርታችን መቆም የሚለው ቃል ማማለድ የሚል ፍቺ ይዞ የሚገኝበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አይተን ነበር፡፡ አያይዘንም የመላእክትን አማላጅነት ከዚሁ ቃል አንጻር ተረድተናል፡፡ በክፍል ሁለት ትምህርታችን ደግሞ ማየት ከሚለው ቃል አንጻር የመላእክትን አማላጅነት እንማራለን፡፡ 

መቆም እንደሚለው ቃል ሁሉ ‹‹ማየት›› የሚለው ቃልም በመጽሐፍ ቅዱስ የራሱ የሆነ አገባባዊ ፍቺ አለው፡፡ በዓይን መለማመጥ፣ ማሳዘን፣ መቆጣት፣ ተስፋ ማድረግ እና ማስፈራራት ይቻላል፡፡ ‹‹የሁሉ ዓይን አንተን ተስፋ ያደርጋል፡፡›› እንዲል፡፡ (መዝ 144.15) ስለዚህ ‹‹ማየት›› መመርመር ወይም ንስሐ መግባት፣ መለመን፣ መጸለይ፣ ተስፋ ማድረግ፣ ማማለድ፣ መስማት፣ መቀበል፣ መቆጣት ወዘተ የሚሉ ፍቺዎች አሉት፡፡

Wednesday, February 1, 2012

የቅዱሳን መላእክት አማላጅነት


 

ቅዱሳን መላእክት አማላጆቻችን ናቸው፡፡ ስለ ቅዱሳን መላእክት አማላጅነት በመጽሐፍ ቅዱስ በስፋት ተጽፏል፡፡ ይህንንም የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በመጥቀስና ትክክለኛ ትርጉማቸውን በምንረዳበት ጊዜ የምናገኘው ነው፡፡

ሐሳቡን በትክክል ለመያዝና ለማጥናት እንዲረዳን የመላእክትን አማላጅነት በስድስት ዋና ዋና መንገዶች ከፍለን ለማየት እንችላለን፡፡

ለዛሬ ከስድስቱ የመጀመሪያውን እነሆ፡-

1. መቆም የሚለውን ቃል ትክክለኛ ትርጉም በመረዳት፡- መቆም የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በልዩ ልዩ ቦታዎች አገልግሎት ላይ ውሏል፡፡ እንደየአገባቡም ትርጉሙ የተለያየ ነው፡፡ መቆም የሚለው ቃል ከያዛቸው ትርጓሜዎች አንዱ ማማለድ የሚል ነው፡፡ መቆም ከተኙበት ወይም ከተቀመጡበት መነሣት፣ በእግር ቀጥ ማለት፣ መጽናት፣ በክብር መቀመጥ ወዘተ የሚሉ ሌሎች ትርጓሜያትም አሉት፡፡ ስለዚህ እንደየአገባቡ ታይቶ ይፈታል እንጂ ሁል ጊዜ ቃሉን በአንድ ዓይነት መንገድ ብቻ መመልከት ከስሕተት ላይ ይጥላል፡፡