እስከዚህ ድረስ በሦስት ተከታታይ ክፍሎች የመላእክትን አማላጅነት ከመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ እየወስድን ተምረናል፡፡ ምንም እንኳን ማስረጃዎቹን ከመጽሐፍ ቅዱስ የጠቀስናቸው ቢሆኑም በምሥጢርና በምሳሌያዊ መንገድ የተቀመጡ ስለነበር ማብራሪያ የተሰጠባቸው ናቸው፡፡
ከዚህ ቀጥሎ የምንጠቅሳቸው ደግሞ በአንጻሩ በግልጽ የተቀመጡ መጽሐፍ ቅዳሳዊ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ የትምህርቱ ፍሰት ከከባድ ወደ ቀላልና ግልጽ ማስረጃ መሆኑን እየጠቆምኩኝ ወደ ትምህርቱ እወስዳችኋለሁ!
ሀ.
ማስታረቅ መንፈሳዊ አገልግሎት ነው፡፡ ይህን የሚክድ ካለም ‹‹የማስታረቅንም አገልግሎት ከሰጠን›› የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ጠቅሰን አፉን እናሲዘዋለን፡፡ (2ቆሮ5.18) መላእክት ደግሞ አገልጋዮች ናቸው፡፡ ይህን ሲያስረዳ መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ቦታ ‹‹መላእክቱን መንፈስ የሚያደርግ፤ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል›› እያለ ሲጠቅሳቸው በሌላ ስፍራ ደግሞ ‹‹ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?›› ይላቸዋል፡፡ (መዝ103.4፤ዕብ1.14) ስለዚህ ማገልገል ማስታረቅን የሚያካትት ከሆነ መላእክት ደግሞ አገልጋዮች ከሆኑ አስታራቂዎች /አማላጆች/ መሆናቸውን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ነገረን ማለት ነው፡፡
ለ.
ይህም ብቻ አይደለም! ዕጣን በጸሎት ይመሰላል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ጸሎቴን በፊትህ እንደ ዕጣን ተቀበልልኝ›› ይላልና፡፡ (መዝ140.2) እንዲህ ከሆነ ‹‹ሌላም መልአክ መጣና የወርቅ ጥና ይዞ በመሠዊያው አጠገብ ቆመ፤ በዙፋኑም ፊት ባለው በወርቅ መሰዊያ ላይ ለቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ ዕጣን ተሰጠው።›› ይላልና፡፡ (ራእ8.3) በዚህ ጥቅስ መሠረት የእግዚአብሔር መልአክ የቅዱሳንን /የምእመናንን/ ጸሎት በዕጣን አምሳል እንደሚያሳርግ ከተረዳን አማላጅነቱን አወቅን ማለት ነው፡፡ አንድ መልአከ ጸሎታችንን ቅድመ እግዚአብሔር የሚያደርስ ከሆነ አማለደ ከማለት ውጭ ምን ትርጉም ይኖረዋል? ያማልዱናል ማለት ልመናችንን ወደ እግዚአብሔር ያደርሱልናል ማለት አይደለምን?
ሐ.
እስራኤላውያን በባቢሎን ምርኮ ለበርካታ አመታት በተሰቃዩ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ስለ እነርሱ በግልጽ ቃል ምልጃ አቅርቧል፡፡ ይህም ምልጃው በዚህ መልኩ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቧል፡- ‹‹የእግዚአብሔርም መልአክ መልሶ፦ አቤቱ፥ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ እነዚህ ሰባ ዓመት የተቈጣሃቸውን ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቼ ነው? አለ።›› (ዘካ1.12) መልአኩ ይህን ልመና ባቀረበ ጊዜ ‹‹እግዚአብሔርም መልሶ ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረው መልአክ በመልካምና በሚያጽናና ቃል ተናገረው።›› ይላል፡፡ (ዘካ1.13)
ታሪኩን ልብ ብሎ ያነበበ ሰው ይህ
‹‹መልካምና የሚያጽናና ቃል›› ምን ይሆን? ማለቱ አይቀርም፡፡ መቼም ‹‹የማትምራቸው እስከ መቼ ነው?›› ለሚለው የልመና ቃል ‹‹ምሬአቸዋለሁ ወይም እምራቸዋለሁ›› ከሚል ውጭ የሚያጽናና ቃል ሊኖር አይችልም፡፡ ይህም በግምት የቀረበ ሐሳብ ሳይሆን መልአኩ ለዘካርያስ ባስተላለፈው የመጨረሻ ቃል ይታወቃል፡፡ ‹‹ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወደ ኢየሩሳሌም በምሕረት ተመልሻለሁ ቤቴ ይሠራባታል በኢየሩሳሌምም ላይ ገመድ ይዘረጋበታል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፦ ደግሞም እንዲህ ስትል ስበክ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከተሞቼ ደግሞ በበጎ ነገር ይረካሉ እግዚአብሔርም ደግሞ ጽዮንን ያጽናናል፥ ኢየሩሳሌምንም ደግሞ ይመርጣል።›› ብለህ ስበክ ብሎ ልኮታል፡፡ (ዘካ1.16-17
መልአኩ የለመነው ምን ነበር?
ምሕረት አልነበርምን? ፈጣሪ ደግሞ በምሕረት ተመልሻለሁ ሲል መለሰ፡፡ የመልአኩ አማላጅነት ተቀባይነት አግኝቷ ማለት ነው፡፡ መላእክት ያማልዳሉ ስንል ይህን የመሳሰሉ ጠንካራና በርካታ መረጃዎችን ከመጽሐፍ ቅዱስ አግኝተን ነው እንጂ ከራሳችን ፍላጎት ተነሥተን አይደለም፡፡
በነገራችን ላይ ይህን ጥቅስ በተመለከተ ገጠመኜን ላውጋችሁ፡፡ አንድ ቀን ከአንድ መናፍቅ ጋር በአጋጣሚ የሃይማኖት ጉዳይ ተነሣና መነጋገር ጀመርን፡፡ ርእሱም ስለመላእክት አማላጅነት ሆነ፡፡ በዚህ ጊዜ ለማስረዳት ይህን ጥቅስ ጠቀስኩለት፡፡ ምን አለ መሰላችሁ? ‹‹መላአኩ እኮ የማትምራቸው እስከ መቼ ነው? አለ እንጂ አልለመነላቸውም፤ ማራቸውም አላለም፡›› ብሎኝ እርፍ፡፡ እኔም እሺ ታዲያ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር? አልኩት፡፡ እርሱም መልሶ ‹‹መቼ ልትምራቸው አስበሃል? ብሎ ቀጠሮ ነው የጠየቀው›› ሲል ደመደመ፡፡ ምንም እንኳን የምንማረው ለመናፍቃን መልስ ለመስጠት ብለን ባይሆንም እንዲህ ዓይነት ዓይን ያወጣ ድርቅና ሊያጋጥማችሁም እንደሚችል አትርሱ፡፡
እንደዚህ መናፍቅ አተረጓጎም መልአኩ የጠየቀው
‹‹እስከ መቼ›› ብሎ ቀጠሮ ከሆነ መልሱ ‹‹በዚህ ጊዜ›› የሚል እንጂ ‹‹በምሕረት ተመልሻለሁ›› የሚል አይሆንም ነበር፡፡ ጥያቄው ምን እንደነበር ከመልሱ በመነሣት ማወቅ ይቻላል፡፡ ሌላው ቋንቋው አማርኛ እስከሆነ ድረስ በሌላም ምሳሌ ማስረዳት ይቻላል፡፡ አንድ አባት በማምሸትና በመስከር ያስቸገረውን ልጁን ‹‹ልጄ እንደዚህ የምትሆነው እስከመቼ ነው?›› ቢለው ቀነ ቀጠሮ ስጠኝ እንጂ አለው ብለን እንደማንፈታው የታወቀ ነው፡፡ ይህ ሐረግ በስድሳ ስድስቱ መጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ ብቻ ከ50 ጊዜ በላይ ስለተጠቀሰ በርካታ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ ስለዚህ ምሳሌውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስናደርገው ቅዱስ ዳዊት ‹‹አቤቱ እስከመቼ ፈጽመህ ትረሳኛለህ?›› እያለ ሲጸልይ ቀን ቅጠርልኝ ማለቱ ሳይሆን አትርሳኝ እንጂ እያለ መለመኑ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ (መዝ12.1) ስለዚህ መልአኩም ‹‹የማትምራቸው እስከመቼ ነው?›› ሲል ‹‹ማራቸው እንጂ፤ አባክህ ማራቸው!›› እያለ እንደለመነላቸው ከምላሹም መረዳት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ቅዱሳን መላእክት በእውነት አማላጆቻችን ናቸው፡፡
ይቆየን!
በዲያቆን ኅብረት የሺጥላ
ቀላል የቤት ሥራ!
ከክፍል
1 እስከ ክፍል 3 ባነበባችሁት የመላእክት አማላጅነት ትምህርት ውስጥ በመጨረሻ ላይ የሚጠኑ ሐሳቦችና ጥቅሶች በአጭሩ ቀርበው ነበር፡፡ ማጠቃለያዎቹ ከዚያው ክፍል ውስጥ የወጡ ነበሩ፡፡ ስንቶቻችሁ ያን ፈጽማችኋል? እስኪ የፈጸማችሁ በዚያው መንገድ ከዚህ በላይ ካነበባችሁት ትምህርት ውስጥ ለሦስቱም አንቀጾች የሚጠናውን ዋና ሐሳብ እና መሪ ጥቅሶቹን አውጥታችሁ በአጭሩ ጻፉአቸው! ልምምዱን ለራሳችሁ አድርጉት!
No comments:
Post a Comment